News News

በንግዱ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገለጸ

በንግዱ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገለጸ

የ2010 በጀት አመት አገራዊ የንግድ ዘርፍ የመደበኛ ስራዎች አፈጻጸም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል፡፡ 

አመታዊ ሪፖርቱ በመፈጸምና በማስፈጸም አቅም ግንባታ፣በንግድ አሰራርና ሬጉሌሽን እና የንግድ ማስፋፊያ ስራዎች ላይ አጽንኦት ሰጥቶ የተገመገመ ነው፡፡

የትኩረት መስክ አንድ ሆኖ በተቀመጠው የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስራዎችን ከመከወን አንጻር በፌደራልና በክልሎች በርካታ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም የንግዱን ዘርፍ ተልዕኮ በብቃት ማሳካት የሚችል የሰው ኃይል ከማዘጋጀትና ከማሰማራት አንጻር ሰፊ ክፍተት  እንዳለበት የተገመገመ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት በንግድ ዘርፍ አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ርብርብ እንደሚደረግ የንግድ ሚኒስተሩ አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ ፣ኦሮሚያ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች በተሻለ ቁመና ላይ የሚገኙ ቢሆንም በታዳጊ ክልሎች ላይ የንግድ ሪፎርም ተግባራትን ከመስፈጸም አንጻር እጥረቶች እየታየ በመሆኑ ሰፊ ስራ መስራትን የሚጠይቅ መሆኑን ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

በንግድ ስራ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ፣ በመለኪያ መሳሪያዎች ቁጥጥር፣ በወጪና ገቢ ምርቶች ጥራት ቁጥጥር በኩል የተከናወኑ ተግባራት በጥንካሬ የተወሰዱ ሲሆኑ አስገዳጅ ደረጃ ወጥቶላቸው ቁጥጥር ሳይደረግባቸው ገበያ ውስጥ ለህብረተሰቡ እየቀረቡ ያሉ ምርቶች መኖር እና ከመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦትና ስርጭት አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

ቀልጣፋና የላቀ የገበያ ማስፋፊያና ትስስር ስርዓት ከመገንባት አንጻር ከጎረቤት አገራትና ከሌሎችም መዳረሻ ይሆናሉ ከሚባሉ አገሮች ጋር ትስስር በመፍጠር ረገድ የተሰራ ስራዎች በጥንካሬ የሚነሱ ቢሆንም በወጪ ንግድ የገቢ መጠን ላይ ችግር እንደሚስተዋልበትና አፈጻጸሙም ከዕቅድ አንጻር ከ54 በመቶ ያልዘለለ መሆኑ በድክመት ተቀምጧል፡፡

ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የወጪ ምርቶች መላክ፣ በአስፈጻሚ አካላት መካከል የሚታየው የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት፣ የገበያ መሠረተ ልማቶች  አለመስፋፋት እና ሌሎችም ለአፈጻጸሙ ማነስ በተግዳሮትነት የጠቀመጡ ናቸው፡፡

የወጪ ንግድ ገቢውን ለማሳደግም ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ጀምሮ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ እና ህገ ወጥ ንግድ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአሰራር ስርአት መፍታት ፣ የአገር ውስጥና የውጪ ገበያ ትስስርን ማጠናከር ፣ በወጪ ንግዱ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት ምጣኔ ሃብት ማሳደግ እና የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስራዎች በ2011 በጀት አመት በትኩረት ሊከናወኑ ከታቀዱት ተግባራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡