News News

አስመጪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሱበት የነበረው ለጥራት ፍተሻ የሚክፍሉት ክፍያ መቅረቱ ተነገረ

 

 

23/01/2011

አስመጪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሱበት የነበረው ለጥራት ፍተሻ የሚክፍሉት ክፍያ መቅረቱ ተነገረ

በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ ምርቶችን ወደሀገር ውስጥ የሚያስገቡ አስመጪዎች የምርቱን ጥራት ለማረጋገጥ ለሚደረግ የላብራቶሪ ምርመራ ይከፍሉ የነበረውን ክፍያ ማስቀረቱን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ

በንግድ ሚኒስቴር የወጪና ገቢ እቃዎች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰምኦን እንደተናገሩት በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ ምርቶች ወደ ሀገር ሲገቡ አስገዳጅ የጥራት ደረጃቸውን ስለማሟላታቸው ናሙና ተወስዶ የላብራቶሪ ምርመራ ለሚደረግበት በሚከፍሉት ከፍተኛ ገንዘብ እና የምርመራ ሂደቱ በሚወስደው ረጅም ጊዜ አስመጪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ የአስመጪዎችን ቅሬታ ለመፍታት እንዲሁም  የንግድ ስርዓቱን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ ይህንን አሰራር በማስቀረት ምርቶቹ የላብራቶሪ ምርመራ ሳያስፈልጋቸው አስመጪዎችም የምርመራና የዋስትና ክፍያ ሳይከፍሉ እንዲያስገቡ ተወስኗል፡፡

 አዲሱ አሰራር በፀሐይ ሀይል ለሚሰራ አንድ ምርት ይከፍሉት የነበረውን 19 ሽህ ብር እና ለዋስትና የሚያሲዙትን 0.5 በመቶ ብር ያስቀረ ነው ያሉት አቶ እያሱ አስመጪዎች ምርቶቹ ከሚመጡበት ሀገር  በአለም አቀፍ የተስማሚነት ምዘና አካላት ተመዝነው የተሰጣቸውን አለም አቀፍ የጥራት ስታንዳርድ ሰርተፍኬት ይዘው ሲቀርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ ማስገባት ይችላሉ ብለዋል፡፡

አቶ እያሱ አያይዘውም ማንኛውም በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ ምርቶች በምርት ሂደት የብራንድ ምዘና/ብራንድ ቴስት/ ተደርጎ በሚሰጣቸው አለም አቀፍ የጥራ ሰርተፍኬት ወደየ ሀገራት የሚሰራጩበት አግባብ አለም አቀፍ አሰራር ስለሆነ በእኛም ሀገር ከመስከረም 18/2011ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ ማሻሻያ የአስመጪዎችን ከፍተኛ ወጪና እንግልት ከማስቀረቱም በተጨማሪ ሸማቹ በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ እንዲጠቀም ያስችላል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

ዘገባው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው