Meet the Minister Meet the Minister

የኢትዮጵያ ንግድ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለውና ሀገራችን ቀደም ብላ የራሷ መገበያያ ገንዘብ በማስቀረፅ ንግድ ያካሄደች ቀደምት የንግድ ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የንግዱ ዘርፍ የሚገኝበት ደረጃ በቀደምት የንግድ ታሪካችን ልክ ሳይሆን በፍጥነት ሊፈቱ የሚገቡ ከንግድ ሰርዓቱን ማዘመን፣ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ከማስፈን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን እና ከአገልግሎት አሰጣጣችን ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች ሙሉ በሙሉ አልተፈቱም፡፡ ስለሆነም የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ንግድ በሚገባበት ጊዜ የሚጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት፣ የንግዱ ማህበረሰብ ከሸማቹ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን፣ ነጋዴው ከነጋዴው ጋር ያለውን ግንኙነት የተሻለ ለማደረግ፣ መንግስትና ህዝብ ከዘርፉ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ እንዲሁም በአጠቃላይ የንግዱ ዘርፍ በባህሪው የሚታይበትን የኢ-ፍሃዊነትና ያለመዘመን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የንግድ የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ የንግድ ስርዓቱን ማዘመን፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የንግድ መረጃዎች በተደራጀ መልኩ ለመንግስትና ለህዝብ እንዲደርሱ ማስቻል ከንግድ ሪፎርሙ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡ የንግድ ዘርፍ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛውን የስራ ዕድል እየፈጠረ የሚገኝና ለኢኮኖሚያችን ከፍተኛውን አበርክቶ ያለው ዘርፍ ነው፡፡ የንግዱ ዘርፍ ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚጠበቀውን ያህል አስተዋፅኦ እንዲያበረክት የንግድ ዘርፍ የለውጥ ሠራዊት በመገንባት የመፈጸም አቅምን ማጎልበት፣ ዘመናዊ፣ፍትሐዊና በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ስርዓት መዘርጋት እና ቀልጣፋና የላቀ የገበያ ማስፋፊያና ትስስር ስርዓት በመገንባት የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን ማሳደግ የሚሉ ሶስት የትኩረት መስኮችን ተለይተዋል፡፡ የወጪ ምርቶችን በጥራት፣ በዋጋና በሚፈለገው መጠን ለዓለም ገበያ በተወዳዳሪነት በማቅረብ የገበያ ደርሻችንን በማሳደግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍ ለማድረግ በኤክስፖርት ዘርፍ የምርትና ግብዓት አቅርቦትን የማሻሻል፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ የማበረታታት፣ የመደገፍ እና የገበያ አድማስ ለማሳደግ የሚያስችል የገበያ ፕሮሞሽን ተግባራት አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ማዕድን ዘርፎች ላይ የተመሰረተው የወጪ ንግዳችን በፍጥነት እንዳይስፋፋና እንዳያድግ በዋናነት የምርት ጥራት ጉድለት፣ በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የአቅርቦት መቀነስ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የፋብሪካዎቻችን የማኔጅመንትና የቴክኒክ አቅም ውስንነት እና የቅንጅታዊ አሠራር መጓደል ችግሮች ቀስፈው ይዘውታል፡፡ ስለሆነም በወጪ ንግድ አፈፃፀማችን የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት የላኪ ድርጅቶችን አቅም ማሳደግ፣ በቂ፣ ጥራት ያለውና ተከታታይ የምርት አቅርቦት እንዲኖርና ፍትሃዊ ንግድ እንዲሰፍን ከአርሶአደሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የንግዱ ተዋናዮች በባለቤትነት ካልተንቀሳቀሱ የአስፈፃሚው አካላት ጥረት ብቻ ምሉዕ አይሆንም፡፡ በየጊዜው የሚፈጠሩ አዎንታዊ ለውጦችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የንግድ ዘርፉን በአግባቡ በመምራት አምራቹን፣ ሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው በትግበራ ላይ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ የህግ ማዕቀፎች ባለቤቶችና ተጠቃሚዎች የሬጉላቶሪ ስራ የሚያከናውኑ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዜጋ በመሆኑ የትግበራው ሂደት የጋራ ርብርብና ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በመጨረሻም የንግዱን ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መላው የአገራችን ህዝቦች የተባበረ ክንዳችሁንና አሻራችሁን በማሳረፍ ለጋራ ልማትና ብልፅግና በጋራ እንሰራ የሚል መልዕክት ለማስተላፍ እወዳለሁ፡፡

 

የኢፌዲሪ ንግድ ና ኢንዱሰተሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር